ህፃናት ሆስቴል ህንፃ ግንባታ ተጠናቆ

📍 ደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ 📅 Apr 08, 2026
Main News
በኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያን የልማት ኮሚሽን በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ የትምህርት ተደራሽነትና ተሳትፎን ማረጋገጥ የሚያስችል የህፃናት ሆስቴል ህንፃ ግንባታ ተጠናቆ በመጋቢት 29/07/2018 ዓ.ም ተመርቆ ለአገልግሎት በቃ። የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያን ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ፓስተር ብርሃኑ ታረቀኝ እንዳሉት፦ የቤተክርስቲያኗ የልማት ኮሚሽን በዳሰነች አካባቢ የህፃናት ሆስቴል ወይም አዳሪ ትምህርት ቤት ለማቋቋም ያነሳሳው ከመንግስት ጎን በመቆም በአካባቢው ያሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተቀርፈው የትምህርት ልማት በዘላቂነት እንዲረጋገጥ ታስቦ ነው ብለዋል።
የልጆች አዳሪ ትምህርት ቤቱ ከነህምያ ጀርመኒ በተገኘ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ግንባታ መደረጉን ፓስተር ብርሃኑ አብራርተው፤ ማዕከሉ የልጆች መኝታ፣ ምግብ፣ ውሃና አጠቃላይ አስፈላጊ ነገሮችን ያሟላ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኮሚሽኑ በመላ ሀገሪቱ ከ175 በላይ የሆኑ ፕሮጀክቶችን ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ እየሠራ እነደሆነ እና እየተከናወኑ ከሚገኙት ተግባራት መካከል ፦በህፃናት እንክብካቤ፣ በጤና፣ በንፁህ የመጠጥ ውሀ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በሠላም ግንባታ፣ አስቸኳይ ድጋፍ እና መሰል ፕሮጀክቶችን ቀርፆ እየሠራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ የዚህ ሁሉ ድጋፍ ግቡ ዜጎች ከጥገኝነትና ከእርዳታ እንዲሁም ከጠባቂነት በመውጣት በየአካባቢው ያሉትን ፀጋዎች በመጠቀም ራሳቸውን እንዲችሉ ታስቦ እንደሆነ ፓስተር ብርሃኑ ገልጸዋል።
በዳሰነች ወረዳ ኦሞራቴ ከተማ ለአገልግሎት የበቃው የልጆች አዳሪ ትምህርት ቤት እና ሁሉ አቀፍ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ተመርቆ ለሥራ እንዲበቃ በሁሉም ዘርፍ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የመንግስት አካላትን ጨምሮ ግለሰቦችና የቤተክርስቲያኗ አገልጋዮችና የኮሚሽኑ ሠራተኞችን አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያን ፕሬዝዳንት ፓስተር ላኮ በዳሶ፤ ለማህበረሰቡ፣ ለራሳቸው፣ ለመንግስትና ለህዝቡ ታማኝና በረከት መሆን የሚችሉ ዜጎችን መፍጠር ትልቅ ራዕይ ይዛ ቤተክርስቲያኗ እየሠራች እንዲሁም
ያለ ትምሀርት ኋላ ቀርነትን ማስቀረት ስለማይቻል ዛሬ ላይ በልጆች ላይ የሚሰጠው ትኩረት ለዚህ ስኬት መነሻ ግብ ነው ሲሉም ገልፀዋል።
የግንባታ ድጋፉን አስተባብረው ወደ ተግባር የቀየሩት የነህምያ ጀርመኒ ዳይሬክተር ፍሬድ ኤርነስ(ዶ/ር)፤ የትምህርት ልማት መሠረት እንዲይዝ ከቤተክርስቲያኗ የልማት ኮሚሽን ጋር በመተባበር በሚያደርጉት ድጋፍ ደስተኞች መሆናቸውን በመግለፅ ፤
ማዕከሉን በመክፈት ሂደት ብዙ ችግሮች ታልፈው ለምረቃ በቅቷል ብለዋል። በቀጣይም በማዕከሉ የሚታቀፉ ልጆች በአግባቡ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የዳሰነች ወረዳ ጤና ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ኝጴይ ኜሪች እና የወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት ምክትል ሀላፊ አቶ ጢሞቲዎስ ሎቻማይ በጋራ እንደገለፁት፤ በወረዳው የኦሞ ወንዝና ቱርካና ሐይቅ ወደ ኋላ ሞልቶ በመፍሰስ በአካባቢው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና አስከትሎ መፍትሔ እየተሰጠ ባለበት የቤተክርስቲያኗ ልማት ኮሚሽን ከመንግስት ጎን በመቆም ላደረገችው አስተዋጽኦ በወረዳው ህዝብ ስም አመስግነዋል።
በማዕከሉ የታቀፉ ልጆች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ልዩ ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግ አረጋግጠው፤ ከቤተክርስቲያኗ የልማት ኮሚሽን ጋር ቅንጅታዊ ሥራው ተጠናቅቆ ይቀጥላል ብለዋል።